ወድቆ በተነሳው ሰንደቅ ዓላማ! አትቀልዱብን!!

Written by Temesgen Desalegn

ባለመሆንና በመሆን መካከል
ሰው አይሻገረው፣ አለ ትልቅ ገደል፡፡
የማይሆነው ነገር፣ ምን ጊዜም አይሆንም
የሆነውም ነገር ከቶ አይለወጥም፡፡…

‹‹የኮሌጅ ቀን ግጥሞች›› (ተገኝ የተሻወርቅ-1950ዓ.ም)

ፐ-እንዴት ያለ ግጥም ነው! ከተፃፈ ከ54 አመት በኋላም ሳይበርድ ሳይነፍስበት የእኛን ዘመኑን ገላጭ ነው፡፡ ፕሮፓጋንዳውን ገላጭ ነው፡፡ የፖለቲካውን ቅጥፈት ገላጭ ነው፡፡ የስርዓቱን ጉምነት ገላጭ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢህአዴግን ገላጭ ነው፡፡ አጋላጭም ነው፡፡

እነሆ! ሰሞኑን ኩማ ደመቅሳ የተባሉ የቀድሞ መንግስት ወታደር፤ በአሁኑ መንግስትየአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ በፓርላማው ፀድቆ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ከታወጀ ሁለት ወር ያለፈውን አዲሱን ‹‹የሊዝ አዋጅ›› በሚመለከት በከተማው ከሚገኙ በርካታ ካድሬዎች እና ጥቂት ገለልተኞች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱም በታ ህሳስ 30 ከምሽቱ ዜና እወጃ በኋላ፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ ተመልክተነዋል፡፡ እናም ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ ክቡራን ሚኒስትሮቻችን የአስተዳደር ዘዬአቸው ዛሬም እንደድሮው የኮሜዲ ዘውግ የሚባል አይነት ሆኖ አገኘሁት፡፡

ይህን ያልኩበትንም ምክንያት እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ እና ደርግ በሚሰሯቸው ስራዎች እና በሚወስዷቸው የሀይል እርምጃዎች አፈፃፀም ላይ ካልሆነ በቀር፣ በውጤቱ መንትዮች እንደሆኑ ምክንያት ደርድረን ተማምነናል፡፡ አዎ! ደርግ ገሎህ በሬሳህ ዙሪያ እየተንጎማለለ ‹‹የፍየል ወጠጤን›› ያቀነቅናል፡፡ በእርግጥ በዚህ፣ በዚህ ኢህአዴግ ጨዋ ነው፡፡ በሬሳህ ላይ አይንጎማለልም፡፡ ይልቁንም ለግድያውም ሆነ ‹‹ለእድሜ ይፍታው›› እስር የህግ አንቀፅ ያፈላልግብሀል እንጂ፡፡ ለሟች ደግሞ የፍየል ወጠጤው ወይም በአንድ ጀንበር የተቀመረው የህግ አንቀጽ ትንሳኤ አይሆነውም፡፡ ወይም ከሞት አያስነሳውም፡፡ እናም መሬትን በአዋጅ መንጠቅም ሆነ፤ አዋጁ ከታወጀ በኋላ አወያይቶ መንጠቅ ልዩነት የለውም፡፡ የደርግ‹‹የመርገጫ ጫማ›› በታጋዮች ተጫምቶ ቀረበ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ሌላ አይደለም፡፡

ለዚህም ነው ኩማ ደመቅሳ እና መኩሪያ ሀይሌ የተባሉ የመንግስት ባለስልጣናት በነጋሪት ጋዜጣ ሳይቀር ታትሞ በተሰራጨ አዋጅ ላይ ያካሄዱት ውይይት በእርግጥም ኮሜዲ ነው ልትለው ትችላለህ እያልኩህ ያለሁት፡፡ በእርግጥ የእነ ኩማ መንግስት ‹‹በፈርሱ ለማጓራት›› ዜጎችን ስራ አስፈትቶ፣ ሲያወያይ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም እንዲሁ አድርጓል፡፡ ታንክ እና መድፍ ተገዝቶ፣ ጦሩ ወደ ውጊያ ወረዳ ከገባ በኋላ በየቀበሌው ህዝቡን እየሰበሰበ ‹‹ኤርትራ መሬታችንን በሀይል ስለወረረች ምን እናድርግ?›› ሲል አወያይቷል፡፡ ይሄ ኮሜዲ ነው፡፡ ኤርትራ ወረራ መፈፀሟ አንድ ነገር ነው፤ ኢትዮጵያም ሉአላዊነቷን ለማስከበር አፀፋዊ ምላሽ መስጠቷ ተገቢ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ጦሯን ወደ አውደ-ግንባር ማዝመቷ ልክ ነው፡፡ ኮሜዲ ነው እያልኩህ ያለሁት ውጊያው ከተጀመረ በኋላ የተከፈተውን የ‹‹እንዋጋ›› ወይስ ‹‹አንዋጋ›› የውይይት መድርኩን ነው፡፡
እነሆ በሌላ ቀን ደግሞ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ ‹‹በይቅርታ መፈታቷን ካደች›› ሲል መንግስት በአንደበቱ ተናገረ፡፡ አስከትሎም ይህንን ክደት እንድታስተባብል የሶስት ቀን ጊዜ ሰጥቻታለሁ፤ አለበለዚያ ይቅርታዋን አነሳለሁ ብሎ ዛተ፡፡ ያ ሶስት ቀንም ያለማስተባበያ አለፈ ተባለና ብርቱካን ታሰረች፡፡ በእርግጥ የብርቱካን መታሰር ፖለቲካዊ ትራጄዲ እንጂ ኮሜዲ አይደለም፡፡ ኮሜዲው ይቅርታው ተነስቶ ብርቱካን ቃሊቲ ገብታ፣ ነገሩ ሁሉ ካለቀ ከደቀቀ በኋላ፣ ኢህአዴግ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞችን ሰብስቦ ‹‹የብርቱካን እስር ተገቢ ነው? ወይስ ተገቢ አይደለም?›› የሚል ውይይት ማድረጉ ነው፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅም ታውጆ፣ በነጋሪት ታትሞ በስራ ላይ ከዋለ በኋላ ነው፣ የሚመለከታቸው አካላት ተሰብስበው እንዲወያዩ የተደረገው፡፡ ይሄንን ነው የሚመሩህ ሰዎች ሲፈልጉ ይደበሩብሃል፣ ሲፈልጉ ይዝቱብሃል፣ ሲፈልጉ ያለህን ይነጥቁሃል፣ ሲፈልጉ ያወድሱሃል፣ ሲፈልጉ ይሰድቡሀል፣ ሲፈልጉ ይደልሉሃል፣ ሲፈልጉ ይሸጡሃል፣ ሲፈልጉም መልሰን ገዛንህ… ይሉሃል ነው የምልህ፡፡
ለምሳሌ እንዴት እንደሚደበሩብህ ማወቅ ከፈለክ ‹‹መሬት የማነው?›› ብለህ ጠይቃቸው፡፡ ሳያቅማሙም እንዲህ ሲሉ ይመልሱልሀል፡፡ መሬትማ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ነው፡፡›› ይሄ ግን ቀልድ እንደሆነ የሚገባህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሚባሉትን በአይንህ ልታያቸው ቀርቶ በህይወት መኖራቸውም በሳይንስ አለመረጋገጡም ሲገባህ ነው፡፡ ወይም የማይዳሰሱ እና የማይጨበጡ፣ የማይታዩ መንፈስ ሲሆኑብህ ነው፤ አሊያም ይህንኑ ባለቤትነቱ የብሄር ብሄረሰቦች…የሆነውን መሬት በሚመለከት ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሀል ያውም ጥቂቱን ብቻ ሰብስበው ሲያወያዩ ነው፡፡ ሆኖም እዚህች ጋ ጥያቄ ልትጠይቅ ትችላለህ፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወይም ብሔር ብሔረሰቦችስ ስለምን በመሬት ጉዳይ አይወያዩም? ብለህ፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ መሰረቴ ያለው በአርሶ አደሩ ውስጥ ነው? የሚለውም ሆነ ሚሊኒየር ገበሬ ፈጠርን ማለቱ እመነኝ የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡

የዚህ ፅሁፍ አላማ የአዲሱን የሊዝ አዋጅ ክፋት እና ደግነት መተንተን አይደለም፡፡ አላማው ኢህአዴግ በየጊዜው ስለምን የፈቀደውን እና ያሰበውን ካደረገ በኋላ፣ በሞተ ነገር ላይ የውይይት መድረኮች አዘጋጅቶ ጊዜ እና የሀገር ሀብት ይፈጃል? የሚለውን በጨረፍታ ማየት ነው፡፡ ይሄ ቀልድ እንጂ ፖለቲካም አስተዳደርም አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ፕሮፓጋንዳ የመሆን አቅም እንኳን የለውም፡፡ ምክንያቱም በሚደረጉት ውይይቶች የሚቀየር ነገር እንኳን ባይኖር፤ አዋጁ ከመታወጁ በፊት ውይይት ቢደርግ፣ ውይይቱ ቢያንስ ፕሮፓጋንዳ የመሆን እድል ይኖረው ነበር፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የሊዝ አዋጅ እንዲታወጅለት ዛሬ ባደረገው ውይይት ገለፀ›› የሚል ማለቴ ነው፡፡ በተቀረ ነገሩ ሁሉ ገጣሚው እንዳለው ነው፡፡‹‹የማይሆነው ነገር፣ ምንጊዜም አይሆንም የሆነውም ነገር፣ ከቶ አይለወጥም›› ወደ ሊዝ አዋጁ እንመለስ፡፡ በጣም ጥሩ፡ ፡ ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ኩማ ደመቅሳ በውይይት ስርዓት አይደለም፡፡ የፓርቲያቸው መግለጫ በመሰለ ንግግር እንጂ፡፡ ‹‹…በአጠቃላይ የሊዝ አዋጁ ተግባራዊ መሆን፤ ለፈጣን አገራዊ ልማትና ለላቀ የህዝብ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስንገባ ብዙሃኑ ህዝቡ እና እውነተኛው ልማታዊ ባለሀብት መጠቀሙና ኑሮውን መለወጡ አይቀርም፡፡ በአንፃሩ ይህ አይነቱ አካሄድ የማይጥማቸውና የማይዋጥላቸው ደግሞ ውስን የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው አይቀርም፡ ፡ በመሆኑም መሬት የመንግስትና የህዝብ አንጡራ ሀብት ነው ብለን በተግባር ስንገባ፣ አንድ ጊዜ መንግስት ወደ እዝ ኢኮኖሚ እየገባ ነው፣ ሲያሻቸው ደግሞ ሌላ ተቀጥላ ማውጣት ተግባሩን ለማደናቀፍ እላይ ታች ማለታቸው አልቀረም፡፡ በእርግጥም ይሄ አዋጅ ተግባራዊ ሲሆን፣ የህዝቦችን የላቀ ተጠቃሚነት፣ ፈጣን ሀገራዊ ልማት ሲያመጣ፣ ያለአግባብ በህገ-ወጥ መንገድ የሚጠቀሙ ሀይሎች መጎዳታቸውና ያልተገባ ጥቅሞቻቸው የሚቀሩባቸው መሆኑ አይቀርም፡፡ በመሆኑም ልማታዊ መንግስታችን፣ ልማታችንን የህዝብ ተጠቃሚነታችንን በፍፁም ለድርድር የሚያቀርብበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ አይገባም፡፡›› እንግዲህ እግዜር ያሳይህ! ይሄ በከንቲባው እሳቤ የውይይት መክፈቻ ንግግር መሆኑ ነው፡፡ ‹‹…በፍፁም ለድርድር የሚቀርብበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ አይገባም፡፡…›› በሚል ወታደራዊ አዋጅ የተከፈተ መድረክ እንዴት ሆኖ የውይይት መድረክ እንደሚሆን ኩማ ደመቅሳ እና መኩሪያ ኃይሌ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡

እነሆም የከንቲባውና የነጋዴዎች ሚኒስትር ቀልድ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ ወታደራዊ መግለጫ በኋላ ጥያቄ ያለው መጠየቅ እንደሚችል ተነግሮ ጥያቄዎች ቀረቡ፡፡ ከአንድ እና ሁለት ጠያቂዎች በቀር፣ የቀረቡት ጥያቄዎች በሙሉ ሲጨመቁ እንዲህ የሚል ትርጓሜ አላቸው፡ ፡ ‹‹መንግስት እስከዛሬ ድረስ ይህንን አዋጅ የት ደብቆት ነው? አዋጁ ዘገየብን፣ አዋጁን ወደነዋል፣ ክቡር ከንቲባው ከአንጀቴ ገብተዋል፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቀብሎታል፣ ተስማምቶታል…፡ .› በእርግጥ በዚህ መሀል ድንገት እንደእርጎ ዝንብ ጥልቅ ያሉ ከመንግስት ፍላጎት ውጪ የሆኑ አንድ እና ሁለት ጥያቄዎች ተነስተው ስለነበር ከንቲባው እና የንግድ ሚኒስትሩ የግዳቸውን መልስ ሰጡበት፡ ፡ ‹‹ሊዙ ከእርስት ይነቅላል፣ አንድ ሰው ሀገሩን ሀገሬ ሊል የሚችለው እርስት ሲኖረው ነው፣ እርስት የሌለው ሀገሬ ሊል አይችልም፣ ነባር ይዞታ ስለምን ወደ ሊዝ ይገባል? ለባለይዞታ የማይረባ ካሳ እየሰጡ አፈናቅሎ፣ ለሌላ ሰው በሊዝ የሚሰጠው ለምንድን ነው?›› የሚሉ ነበሩ ጥያቄዎቹ፡፡ እናም የመጀመሪያው መላሽ መኩሪያ ሀይሌ ተጨንቀው፣ ተጠበው ቀለዱ፡፡ ወይም መልስ ሰጡበት፡፡ መለሱ ያልኩት ሌላ ቃል ስላጣሁ እንጂ እሳቸውማ ያሉት እንዲህ ነው ፡-

‹‹…እንዲህ አይነት መድረኮች ሲከፈቱ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮች ካሉ በግብአትነት መውሰድ ባልተቋረጠና እንደባህልም እንደ አሰራርም፣ የሚሰራበት ባህል ነው፡፡ …አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ከህብረተሰቡ ከነጋዴው ማህበረሰብ አስተያየት መቀበል የነበረብን ነው የሚመስለኝ፣… ይሄንን እንደክፍተት እናየዋለን በእኛ በኩል …እንደ ልምድ እንደ ተሞክሮ እንወስደዋለን፡፡ በቀጣይ እንደዚህ አይነት ህጎች ሲወጡ ነዋሪው እየተሳተፈ፣ የንግዱ ህብረተሰብም እየተሳተፉ የሚሄዱበትን መንገድ እንፈጥራለን፣ በቀጣይ… ወዘተ›› ከሚለው ቀልዳቸው ውጪ (መቼም ስልጣን ከያዘ 21ኛ አመቱን የያዘ መንግስት፣ አዋጅ ሲያወጣ ከህዝቡ ጋር መመካከር እንዳለበት ዛሬ ነው የገባኝ ብሎ በቀጣይ… በቀጣይ… የሚል አይመስለኝም፡፡ ወይም ንፋስ የአመጣቸው አንዳንድ ሚንስትሮች ለስርአቱ አዲስ ስለሆኑ ቀድሞ ለነበረው የፖለቲካ ጨዋታ ግድ ስለሌላቸው ይሆን?) መኩሪያ ሀይሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአነጋገር ዘይቤ እንደ አይዶል ሾው ተወዳዳሪ እያስመሰሉ (በነገራችን ላይ ‹‹አራት ነጥብ›› የምትለውን ቃል ካለመጠቀማቸው ውጪ ማስመሰሉ ተሳክቶላቸዋል፡፡ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ አራት ነጥብ የምትለዋን ቃልም ተጠቅመው እንደምናይ ተስፋ አደርጋለሁ) የመለሷቸው መልሶች በጭራሽ ከጥያቄው ጋር የማይገናኝ ነው፡ ፡ የሊዝ አዋጁ መሬቴን፣ እርስቴን ነጠቀኝ የሚል ጥያቄ በተነሳበት መድረክ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሉአላዊነቱን ለማስከበር፣ ለሀገሩ ዳር ድንበር የከፈለው መስዋዕትነት…›› የመሳሰሉት ምላሾች እንዴት ሆነ ው ከሊዝ ጋር እንደሚገናኙ መቼም ከሚንስትሩ ውጭ ያወቀ ቡዳ ነው፡፡

ሌላው ከሚኒስትሩ ኩመካ ውስጥ ከልብ ያሳቀችኝ ቀልድ እንዲህ የምትለው ነች፡ – (በነገራችን ላይ እሳቸው ስለሊዝ አዋጁ አስፈላጊነት ሙያዊ ትንታኔ መሰጠታቸው መሰለኝ) ‹‹የሊዝ አዋጁ ሁለት ዋና ዋና ፋይዳዎች አሉት፡፡ አንደኛው፡- ባለሀብቱ መሬት ሲፈልግ በቅልጥፍና እንዲያገኝ ያስችላል፤ ሁለተኛው መሬት ለባለሀብቱ በፍጥነት እንዲቀርብ ያደርጋል…፡፡››
እንግዲህ ለክቡርነታቸው ‹‹በቅልጥፍና›› እና ‹‹በፍጥነት›› የሚሉት ቃላቶች ሁለት የተለያዩ ከፍተኛ ጥቅሞች መሆናቸው ነው፡፡ በእርግጥ ሚኒስትሩ በዚህች ቀልድ ብቻ አላቆሙም፡ ፡ እንግዲህ ልብ በል! ውይይቱ ‹‹የሊዝ አዋጁ ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ?›› በሚል ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ እናም ክቡርነታቸው አዋጁን ጎጂ ነው ሲሉ የተቃውሞ (የቅሬታ) ጥያቄ ላቀረቡ ጠያቂዎች ስለጠቃሚነቱ ሲያስረዱ ‹‹ከአዋጁ ቀጥሎ›› አሉ ‹‹ደንብ ይወጣል፣ ከደንቡ በኋላ የአፈፃፀም መመሪያ ይወጣል፡፡ ከአፈፃፀም መመሪያ በኋላ የማንዋል መመሪያ ይወጣል፣ ከማንዋል መመሪያ በኋላ…›› ኧረ! በባንዲራው ይሁንባችሁ! ቢያንስ አትቀልዱብን፡፡

እሺ! ደህና!! አምባገነንነታችሁን እንቻለው፣ የኮሮጆ ግልበጣውንም እንሸከመው፣ አፈናውንም እንቀበለው፣ ሙስናውንም አይተን እንዳላየ እንለፈው፣ አድሎአዊ አሰራሩንም ይሁን እንበል፣ የፈጠራ ውንጀላውን እና የፈጠራ ክሱንም እንታገሰው… ቢያንስ ግን አትቀልዱብን፡ ፡ የኩማ ደመቅሳ እና የመኩሪያ ሀይሌ አይነት ተዋናዮቻችሁንም በራሳችሁ መድረክ እንዲቀልዱ አድርጓቸው፡፡ እኛን ግን ተዉን! ኑሮ የቀለደብን ይበቃናል፡፡ የፍትህ ስርአቱ ያላገጠብን ይበቃናል፡ ፡ ምርጫው ያፌዘብን ይበቃናል፡፡ 11 በመቶው ኢኮኖሚ ያሾፈብን ይበቃናል፡፡ የዋጋ ንረት ጢባ ጢቦ የተጫወተብን ይበቃናል፡፡

የሆነ ሆኖ አንድ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ‹‹አዋጁ አስፈላጊ ነው ወይስ አያስፈልግም?›› በሚል የሚዘጋጁት የውይይት መድረኮች ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው ቁጣ እና ጥላቻ እንዲጨምር ከማድረግ ውጪ አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡ ምክንያቱም ሲጀመር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀደቀ የተባለ አዋጅ እንደገና ተመልሶ ወደ ህዝብ መውረዱ አስፈላጊነቱ ለማንም ግልፅ አይደለም፡፡ አሊያም በተወካዮች ምክር ቤት የሚሰማው የአንድ ፓርቲ ድምፅ ነው፣ የህዝቡ ቅሬታ አይቀርብም፣ የሀሳብ ፍጭት የለም ብላችሁ ልክ አንደኛ እንደተራው ዜጋ የምታምኑ ከሆነ፣ ሁለት አማራጮች አሏችሁ፡፡ የመጀመሪያውና ጠቃሚው አማራጭ ፓርላማውን በትኖ፣ አዲስ ፓርላማ በምርጫ ማቋቋም ነው፡፡ ይሄን ከመረጣችሁ ወዲህም ታሪክ ታሰራላችሁ፡፡ ሁለተኛው ምርጫ ግን ምንም አይነት አዋጅና ህግ በፓርላማ ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት እንደ አቴናውያን የየከተማውን ህዝብ በየአደባባዩ ሰብስቦ ማወያየት ነው፡፡ ይሄ ለቀልዱም ይመቻል፡፡

ከዚህ በተረፈ የምታወጧቸው አዋጆች እና እቅዶች በሙሉ ጥቂት ጥቅመኞች ተቃወሙት እንጂ ህዝቡ ተቀብሎታል የምትሉትን፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ህዝብ ከኢህአዴግ ፍቅር ይዞታል፣…. ገለመሌ የሚለውን ፕሮፓጋንዳ እንደ እርስት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ማድረጉ የሚበጅ አይመስለኝም፡፡

ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት በዛ የጥላት ዘመን የነበረው የፕሮፓጋንዳ ስራ ከዛሬው ጋር የአንድ እናት ልጅ ነው፡፡ በጋዜጣ የሚወጣውም ከርዕስ አመራረጡ ጀምሮ የብእር አጣጣሉም አልተቀየረም፡፡ የምር እንነጋገር ከተባለ ደግሞ ቅዳሜ ጳጉሜ 3 ቀን 1932ዓ.ም የታተመው ‹‹የቄሳር መንግስት መልክተኛ›› የሚባለው የአማርኛ ጋዜጣ በፊት ገፁ ላይ እንዲህ የሚል ዜና ይዞ መውጣቱን ለዚህ ፅሁፍ ማስረጃ ይሆን ዘንድ እንየው፡፡ መልካም! ዜናው እንዲህ ይላል፡– ‹‹ጄነራል ናዚ በሱማሌ አገር ስላደረጉት ታላቅ ድል የአዲስ አበባ ህዝብ ታማኝነቱንና ደስታውን ገለጠላቸው፡ ፡››

ዝርዝር ዘገባው ቀጥሎአል፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያ በጣሊያን አስተዳደር ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጠንካራ መሆን እንደቻለች አንዱ ምስክር ህዝቡ /ብሔር ብሔረሰቦች/ ተቀራርበው ተከባብረው እየኖሩ እንደሆነ ያትትና፣ ራስ ሀይሉ ‹‹ዛሬ በዚህች ሰዓት በክቡርነትዎ ፊት ቀርቤ በኢትዮጵያ ስም ሆኜ በልዑል እምልዑላን በኢትዮጵያ ቄሳር እንደራሴ ትእዛዝ ስለሰሩት የድል አድራጊነት ስራ ምስጋና ለመናገር በመቻሌ ለእግዚአብሔር ምስጋናዬን አቀርባለሁ›› ማለታቸውን ይገልፃል፡፡

እነሆ የኢህአዴግም ዜና ቀጥሏል፡ ፡ …መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በምርጫው ተሳተፈ፡፡ ድምፁንም ሙሉ በሙሉ ለኢህአዴግ ሰጠ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ የሊዝ አዋጁን እንደወደደው ገለፀ፡፡ የነጋዴዎች ማህበራትም አዋጁን እፁብ ድንቅ አሉት፡ ፡ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ኢህአዴግን እንደግል አዳኛቸው ተቀበሉት፡ ፡ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ‹‹በኢህአዴግ ጊዜ የለም ትካዜ›› እያሉ ጨፈሩ፡ ፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሊዝ አዋጁ ‹‹እልል በቅምጤ››ነው አሉ፡፡
እደግመዋለሁ፡፡ ወድቃ በተነሳችው ሰንደቅ ዓላማ! አትቀልዱብን!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>

Visit Us On FacebookVisit Us On Youtube